የክልሉ መንግስት የአርሶ እና አርብቶ አደሩን ህይወት መለወጥ ላይ አበክሮ እየሰራ ነው-ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ

0 minutes, 0 seconds Read
Share To Social Media

ቦረና ሰኔ 25/2015(ኢዜአ)፦ የክልሉ መንግስት የአርሶ እና አርብቶ አደሩን ህይወት መለወጥ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለፁ።

በዞኑ ሞያሌ ወረዳ የተመረቀው የቡርቁቄ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ክልሉ በድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አርብቶ አደሮች ድርቁን ተቋቁመው በዘላቂነት የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማለት የቀረጸው “የፊነ ፕሮጀክት” አካል ነው ተብሏል።

የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ በዚሁ ጊዜ በአርብቶ አደሮቹ አካባቢ ከተጀመሩት 72 የፊነ ፕሮጀክቶች ውስጥ 18ቱ በቦረና ዞን የተጀመሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህም መካከል ዛሬ የተመረቀው የቡርቁቄ ግድብ አንዱ ነው ብለዋል።

በተለይም በክልሉ በተከሰተው ድርቅ የሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ከተደረገው የዕለት ዕርዳታ ባለፈ በዘላቂነት ከችግሩ ለመውጣት የውሃና የመስኖ ልማት ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ብለዋል።

የቡርቁቄ መስኖ ልማት ፕሮጄክት ለህዝባችን ልማት ገንብተን አጠናቀን ወደ አገልግሎት የማስገባት ቃል የገባነውን በተግባር ያረጋገጠ ነውም ብለዋል።

በዞኑ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ረዥም አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ህብረተሰቡ በሙሉ አቅሙ መስራት የሚያነሳሳው መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የቦረና ህዝብ የአካባቢውን ሰላም በሙሉ አቅሙ በመጠበቅ ልማቱ ላይ ርብርብ ማድረግ አለበት ብለዋል።

የኦሮሚያ አርብቶ አደርና መስኖ ልማት ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ በበኩላቸው የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዜይቤ ለመለወጥ በአካባቢው ያለውን የውሃ ሀብትና ዝናብ በማቆርና በማልማት ለመጠቀም እየሰራን ነው ብለዋል።

በዚህም በአርብቶ አደሩና የዝናብ እጥረት ያላቸው የክልሉ ዞኖች “የፊነ ፕሮጀክቶች” ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።

ከእነዚህ ውስጥ በቦረና ዞን ከ3 ቢሊዮን ብር 9 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።

በዞኑ 18 ፕሮጄክቶች በፊነ ፕሮጄክቶችና በመደበኛ ግንባታቸው እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።

ግድቦቹ በደለል እንዳይሞሉ የተፋሰስ ልማት፣ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የቦረና ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱሰላም ዋሪዮ እንደገለፁት ድርቁ ያስከተለውን ጊዜ አልፈን ዛሬ የጀመርነውን ልማት እውን አድርገናል ብለዋል።

ትልቁ ችግር የነበረው ውሃና የእንስሳት መኖ ነው ያሉት አስተዳዳሪው ችግሩን ለመቅረፍ በቦረና ዞን 18 ፕሮጀክቶች ተገንብተው እየተመረቁ ይገኛሉ ብለዋል።

ትልቁ ውጤት አሁን የመጠጥና የመስኖ ውሃ አግኝተናል ያሉት አቶ አብዱሰላም፤ ውሃውን በመንከባከብና በመጠበቅ ለልማት ማዋል አለብን ነው ያሉት።

በተለይ በግድቡ አካባቢ ያሉ ቀበሌዎች ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በተፋሰስ ልማት፣ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ በመስራት መጠበቅ አለብን ብለዋል።

የሞያሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም አብዲ በበኩላቸው ድርቁ ባስከተለው ችግር ብዙ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል።

አሁን በወረዳው ቦኮላ ቀበሌ የተመረቀው የፊነ ኦሮሚያ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ድርቁ የሚያስከትለውን ችግር ከመቋቋም ባለፈ ወደ እርሻ ልማት ለመግባት የሚያስችለን ነው ብለዋል።

ዛሬ ግድቡ ውሃ ይዞ አይተናል፤ በቀጣይ አካባቢውን በሰብል በማልማት የህዝቡን ፍላጎት እውን እናደርጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

Similar Posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *